Our History

አጭር ሕይወት ታሪክ

ጳውሎስ ዘኢየሱስ (አባ ተክለማርያም ኃይሉ ገብረሚካኤል): ወላጅ አባታቸው አዘውትረው “ተክለማርያም” ብሎ ቢጠሯቸውም አብዛኛው ሰው እና ራሳቸው የሚወዱት ስም ግን እናታቸው ገና በልጅነታቸው ያወጡላቸውን “ጳውሎስ” የሚለውን ስም ነው።

ትውልድ

የጳውሎስ ዘኢየሱስ የትውልድ አገራቸው በሰሜናዊው የኢትዮጵያ ክፍል ሲሆን እናታቸውና አባታቸው የሁለት የእዚያው አካባቢ ተወላጆች ናቸው።

ትምህርት

አባታቸው የተማሩ ቄስ ስለ ነበሩ ገና በልጅነታቸው ግብረ ዲቁና አስተማሯቸው። እርሳቸውም የግብረ ዲቁናውን ሙያ ተፈትነው ካለፉ በኋላ የዲቁናውን መዓርግ ከሊቀ ጳጳሱ ከአቡነ መርሐ ክርስቶስ ተቀበሉ።

ከዚያ በኋላ በዲቁና ሙያቸው በደብረ አባይ መዝገበ ቅዳሴ ሲቀድሱ ልዩ የሆነ ፀጋ ስጦታ ስለ ነበራቸው ይህንን ያስተዋሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉበት ሲነግሯቸው በዲቁና ለአንድ ዓመት ያህል ካገለገሉ በኋላ ወደ ዜማ (ድጓ) ትምህርት ቤት አመሩ።

ጾመ ድጓዉንና ድጓዉን ለመማር ዜማ ትምህርት ቤት በመግባት ጾመ ድጓውንና ድጓውን በ3 ዓመት አጠናቀቁ። ቅኔውን ለመማር ደግሞ ቅኔ ትምህርት ቤት ገብተው የቅኔውን ትምህርት በ4 ዓመት አጠናቀቁ። በመቀጠልም አቋቋሙን ለመማር አቋቋም ትምህርት ቤት በመግባት አቋቋሙን በ5 ዓመት አጠናቀቁ። ዝማሬንና መዋሥዕቱን ለመማር ዝማሬ ወመዋሥዕት ትምህርት ቤት ገብተው ዝማሬንና መዋሥዕቱን በ2 ዓመት አጠናቀቁ። ሥነ መለኮትን ወይም መጽሐፍ ቅዱስን (ብሉይንና ሐዲስን) ለማወቅ ደግሞ አዲስ አበባ መንፈሳዊ ኮሌጅ በመግባት የሥነ መለኮት ትምህርታቸውን በ5 ዓመት አጠናቀቁ። ከጥቂት ዓመታት በኋላም ደቡብ አፍሪካ በሌላ የሥነ መለኮት ትምህርት ቤት በመግባት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ለ3 ዓመታት ተምረው አጠናቀቁ። ይህም ማለት በትምህርት ብቻ 22 ዓመታት አሳልፈዋል።

የሕይወት ምስክርነት (በራስ አንደበት)

ጊዜው የሥነ መለኮት ትምህርቴን ላጠናቅቅ አንድ ዓመት ሲቀረኝ ነበር፤ ነገሩ እንደዚህ ነው፤ በመንፈሳዊ ኮሌጅ እያለሁ የእረፍት ጊዜዬን የማሳልፈው በዋልድባ ገዳም በአብረንታት ነበር። በዚያ ገዳም ሱባዔን ይዤ በሥራ፣ በፆም በጸሎት፣ በብዙ ተጋድሎ በቀን ቢያንስ እስከ 1000 ጊዜ በመስገድ በልፋት ለመጽደቅ በምታገልበት ጊዜ ነበር ጌታችን ኢየሱስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ደሙ ከሁለት እጆቹና ከእግሩ እየፈሰሰ የተገለጠልኝ። ከተገለጠልኝ በኋላ በጉልህ ድምፅ፡- “ልጄ እዚህ ምን ትሠራለህ!? ውጣና ከዚህ በኋላ ሊሆን የሚያስፈልገውን ነገር አሳይሃለሁ” አለኝ። እንደ ገናም በሦስተኛው ቀን ልክ እንደ መጀመሪያው ተገልጦ ከዘላለም ሞት ካመለጥኩ በኋላ ወንጌልን በመስበክና በመመስከር ሌሎችን ማስመለጥ እንዳለብኝ ተናገረኝ።

ከዚያ በኋላ እ.ኤ.አ. በ2007 ዓ.ም በሥነ መለኮት በባችለር ዲግሪ ተመረቅሁ። ወዲያውም በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ሊቀ ጳጳስ የቁምስና መዓርግና “መልአከ ምሕረት” የሚል የሥልጣን መዓርግ ተሰጠኝ። በተጨማሪም በብፁዕ አቡነ ኤዎስታቴዎስ ሊቀ ጳጳስ “መልአከ ገነት” የሚል የሥልጣን መዓርግ ተሰጠኝ። በአዲስ አበባም በታላላቅ ካቴድራሎች ለጥቂት ጊዜ ሥልጣን ተሰጥቶኝ ማስተዳደር ጀመርኩኝ። ከዚህ በኋላ ሲኖዶሱ ባለኝ ትምህርትና የሙያ ብቃት መርጦኝ የደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ካቴድራል መድኃኔ ዓለም ዋና አስተዳዳሪ አድርጎ ሾሞ ላከኝ።

ነገር ግን ለአንድ ዓመት ያህል ካቴድራሉን በኃላፊነት ካስተዳደርኩኝ እና ሕዝቡን ወንጌል ካስተማርኩኝ በኋላ እንዲሁም “እውነተኛው እምነት በእውነተኛው አማኝ ሲገለጥ” የተሰኘውን መጽሐፍ ጽፌ መጽሐፉን ካሰራጨሁ በኋላ በደረሰብኝ ጫና ምክንያት ከቤተ ክርስቲያኒቱ ወጣሁ፤ ወንጌልን ስሰብክላቸው ከነበሩት መካከል ከ500 በላይ የሚሆኑት ሰዎች ከእኔ ጋር በመውጣት እንደ እኔ ጌታን ተቀብለው ከዘላለም ሞት አመለጡ።

ከዚህ ነገር በኋላ ሰይጣን የእምነቱን ተከታዮች በመጠቀም እኔን ለመግደል ቀን ከሌት ይተጋ ጀመር፤ ሆኖም ግን መንፈስ ቅዱስ ለአራት ዓመታት ያህል በአንድ የሥነ መለኮት ትምህርት ቤት መቆየት እንዳለብኝ ምሪት እና ዕድል ሰጠኝ። በእርሱ እርዳታም ከጠላቶቼ ተሰውሬ ለአራት ዓመታት ያህል የእግዚአብሔር እስትንፋስ የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስ እንደገና ተምሬ አጠናቀቅሁ።

ተልእኳችን ፡- “እንዲህም አላቸው፡— ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፤ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ።” (የማርቆስ ወንጌል 16:15) በሚለው ቃል መሠረት ኢየሱስን (ወንጌልን) ለዓለም ሁሉ ማድረስ እና በጌታ የዳኑትን እያስተማሩ (እየተከሉ) ለደቀ መዝሙርነት ማብቃት ነው ። (ማቴዎስ 28÷19-20) ።

ስለሆነም በሰማይና በምድር ያለው ሁሉ በክርስቶስ እንዲጠቀለል ይህ “መዳን በክርስቶስ” አገልግሎት ከሁሉም ቅዱሳን ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ የበኩሉን ክርስቲያናዊ ኃላፊነት እየተወጣ ይገኛል። ይህንን የምታነቡም ሰዎች ቃሉ “በዘመን ፍጻሜ ይደረግ ዘንድ ያለው አሳቡም በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል ነው” ስለሚል (ወደ ኤፌሶን ሰዎች 1:10) በክርስቶስ ያልተጠቀለሉት በክርስቶስ እንዲጠቀለሉ በተሰጣችሁ ጸጋ ከእኛ ጋር ወንጌል ሥሩ። ኢየሱስ ሊመጣ በደጅ ነው! “ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፤ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል” እንደሚል (2ኛ የጴጥሮስ መልእክት 3:9) ጌታ የዘገየው ያልዳኑት እስኪድኑ ድረስ ብቻ ነው። ለዚህ ሥራ ደግሞ የተመደብን እኛ ነን። መክሊታችንን እንድናፈራበት ጌታ ይርዳን! (ማቴዎስ 25÷14-30 ፤ ዳንኤል 12÷3) ።

የራእዩ ባለቤት እግዚአብሔር ሲሆን የራእዩ ተቀባይ እኔ ጳውሎስ ዘኢየሱስ (አባ ተክለማርያም ኃይሉ ገብረሚካኤል) በሐዋርያት ሥራ 4÷12 ባለው ሕያው ቃል ላይ ተመሥርቶ “መዳን በክርስቶስ …” በሚል ስም የመዳን ቲቪ ራእይ ከእግዚአብሔር ተቀበልኩ፡፡ ወቅቱ ጌታን ከተቀበልኩ በኋላ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ የአራት ዓመት ሥነ መለኮት ትምህርቴን ካጠናቀቅሁ በኋላ እ.ኤ.አ. ጥቅምት 27/2016 ነበር፡፡ አስታውሳለሁ … ዕለቱም “ሐሙስ” በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከሌሊቱ 9:00 ላይ ለመቁጠር የሚያዳግት እጅግ ብዙ የሆነ ሕዝብ ተሰብስቦ ወንጌልን ስሰብክና እየሰበክሁ እያለሁም የሁሉም ሰው ልብስ ወደ ሚያንፀባርቅ ነጭ ልብስ ተቀይሮ አየሁ፡፡ ከራእዩም በኋላ፡- “በዚህ አገልግሎት ከ2 ቢሊየን በላይ ነፍሳት ወደ መንግሥቴ አፈልሳለሁና ታጠቅ፤ ተዘጋጅ” የሚል ነጎድጓድ የሚመስል ታላቅ ድምፅ ሰማሁ። ወዲያውም የሆነውን ነገር ጻፍኩት።

ካየሁት ራእይም የተነሣ ውስጤ ከዚያ በፊት በማላውቀው ኃይልና ደስታ ተሞላ። ይህንን ራእይ ካየሁበት ጊዜ ጀምሮ የተገለጠልኝን ወንጌል ለመመስከር በበለጠ ድፍረትና ብርታት ተሞላሁ። በመሆኑም በታላላቅ ኮንፍራንሶች መመስከር ስጀምር አገልግሎቱም በሶሻል ሚዲያ ሲቀጣጠል ከአገልግሎቱ የተነሣም ብዙ ነፍሳት ከዘላለም ሞት ማምለጥ ሲጀምሩ ሰይጣንም በሚጠቀምባቸው ሰዎች እኔን ለመግደልና ለማሳደድ ታጥቆ ተነሣ።

ስለሆነም አገልግሎቱን ከጀመርኩ ከአንድ ዓመት በኋላ እ.ኤ.አ. መጋቢት 17/2017 እንደ ወንጀለኛ ሲከታተሉኝና ሲሰልሉኝ ከዋሉ በኋላ በደቡብ አፍሪካ በጆሃንስበርግ “ኢስትጌት” በሚባል የመገበያያ ሱቆች ያሉት አዳራሽ ፓስተር ግርማይ ከሚባል ኤርትራዊ እና ፓስተር ጆኤል ከሚባል ኢትዮጵያዊ ጋር እያለሁ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ አንድ ሰዓት ገደማ ከገበያው አዳራሽ ወጥተን ወደ መኪና ማቆሚያው ክልል ስንገባ ከ40 በላይ የሚሆኑ ክፉ ተልዕኮ ያላቸው ሰዎች ሦስት ሽጉጥ በእኔ ላይ በመደቀን፣ ሌሎቹም ካሜራ በመቅረፅ፡- “ዛሬ ከዚህ ሞት የምታመልጠው አራቱን ጥያቄዎቻችን ከመለስክ ብቻ ነው፤ 1ኛ. “መዳን በድንግል ማርያም ብቻ ነው” ካልክ፤

2ኛ. “ድንግል ማርያም አማላጅ ናት” ካልክ፤

3ኛ. “ኢየሱስ አያማልድም” ካልክ፤

4ኛ. ልብሳችንን ትመልሳለህ ወይስ አትመልስም?” “እነዚህ አራቱን ጥያቄዎች በትክክለኛው መንገድ ከመለስካቸው ከሞት ታመልጣለህ፤ እኛ እንደምንልህ ካልመለስካቸው ግን እዚሁ እንደፋሃለን” አሉኝ፡፡ እኔም ስመልስ፡- “ጊዜው ከሆነና ጌታ ከፈቀደላችሁ ግደሉኝ እንጂ

#1. መዳን በኢየሱስ ብቻ ነው። ማርያም አታድንም።

#2. ማርያም አታማልድም።

#3. እውነተኛው አማላጅ ኢየሱስ ብቻ ነው።

#4. የቁምስናው ልብሰ ተክህኖም “ኢየሱስን ስበክበት” ተብሎ በአደራ ስለ ተሰጠኝ አልመልስም” አልኩኝ፡፡ በእንደዚህ ሁኔታ እያለን ፖሊሶች ደረሱና ሰዎቹ ተበታተኑ።

ፖሊሶቹም የያዟቸውን ሰዎች መኖሪያ ፈቃዳቸውን ከወሰዱባቸው በኋላ በነገታው ጠሩኝና በተለይ ኢንስፔክተሩ፡- “እነዚህን ሁሉ ከእዚህ አገር በግዴታ እንዲወጡ እንድናደርጋቸው ፈርም” ሲለኝ “በጭራሽ! አልፈርምም! ከእዚህ አገር በግዴታ እንዲወጡ እንዲደረጉም አልፈቅድም” አልኩት፡፡ “ለምን?” አለኝ፤ “እኔ እንደዚህ ከተበቀልኳቸው በጌታ ዘንድ ዋጋ የለኝም” ስለው እስከ አሁን የማይረሳኝ፣ ኢንስፔክተሩ ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ፡፡ “በውኑ በዚህ ዘመን እንደ እነ ጳውሎስ ዓይነት አገልግሎት አለ ማለት ነው!?” አለ። ከዚያ በኋላ መኖሪያ ፈቃዳቸውን ሰጥቶ አሰናበታቸው።

ይህ ሳምንት እንኳን ሳይሆነው እ.ኤ.አ. መጋቢት 19/2017 እንደገና በገንዘብ የተገዙ ነፍሰ ገዳዮችን እኔ እቤት ባልነበርኩበት ሰዓት መኖሪያ ቤቴ ድረስ በመላክ ቀደም ሲል “እውነተኛው እምነት በእውነተኛው አማኝ ሲገለጥ” በሚል ርዕስ ያሳተምኩትን መጽሐፍ የቤቴን በር አስሰብረው፣ ከ300 በላይ የሚሆኑ ቅጂዎችን አስዘርፈው በመድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ በቤንዚን በማቃጠል ተንቀሳቃሽ ምስሎቹን ማሕበራዊ መገናኛ ብዙኀን ላይ ለቅቀዋቸዋል። ሁለቱም ቪዲዮዎች እዚህ የመረጃ መረባችን (ዌብሳይታችን) ውስጥ ይገኛሉ።

ከዚህም በኋላ በብዙ መከራና ፈተና እያለፍኩም ጌታ እየጠበቀኝ ለአንድ ዓመት ያህል በኤልሻዳይ ቴሌቪዥንም አማካይነት አገልግያለሁ። በዚህ አገልግሎትም ቁጥራቸው እጅግ ብዙ የሆኑ ሰዎች ጌታን ተቀብለው ከዘላለም ሞት አምልጠዋል። እ.ኤ.አ. ከ2017 እስከ 2018 ዓ.ም በብዙ ውጣ ውረድና ራሴን ከማሕበራዊው ኑሮ በማግለል ከአንዱ ከተማ ወደ ሌላኛው ከተማ እየሸሸሁ ባገኘሁት የአገልግሎት ዕድል ሁሉ እየተጠቀምሁ በድብቅ አገለግል ነበር።

ነገር ግን እ.ኤ.አ. በ2018 ዓ.ም ጌታ በሰጠኝ ራእይ መሠረት መዳን በክርስቶስ በደቡብ አፍሪካ መንግሥት ሕጋዊ ሆኖ እንዲመዘገብ አደረግሁ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እ.ኤ.አ. እስከ 2022 ዓ.ም በፌስ ቡክ እና በዩ ቱዩብ በማደርገው ሳምንታዊ አገልግሎት ከ8,500 በላይ የሚሆኑ ኤርትራውያን እና ኢትዮጵያውያን ድነዉበታል። አሁን ግን ጌታ ረድቶን የአየር ሳተላይት ቲቪ ተከራይተን በኤርትራ ምድርና በኢትዮጵያ ምድር የ24 ሰዓት የወንጌል ስርጭቱን በቴሌቭዥን በመልቀቅ ሕዝባችንን ከዘላለም ሞት ለመታደግ ተዘጋጅተናል።

በሰማይና በምድር የሚገኙትን ፍጥረታት ሁሉ የፈጠረ፣ ሁሉን ቻይ፣ ታላቅ፣ ዘለዓለማዊ፣ ፍጹም እና የማይለወጥ፤ ራሱን በሦስት አካል፡ በአብ በወልድ እና በመንፈስ ቅዱስ የሚገልጥ በአንድ አምላክ ታምናለች።

ዘፍጥረት 1፡26፤ ዘዳግም 6፡4-5፤ መዝሙር 89 (90)፡2፤ መዝሙር 138 (139) 7-21፤ መዝሙር፤ ትንቢተ ኢሳያስ 40፡28፤ ትንቢተ ሚልኪያስ 3፡6፤ የዮሐንስ ወንጌል 17፡11።

እግዚአብሔር አብ፡ በፍቅሩ፣ በምህረቱ እና በቃሉ በኩል ለሰበዓዊ ፍጡር ሁሉ በገባው ቃል ኪዳን መሰረት የሰጠውን የተስፋ ቃል በመብቅ የአምሳሉ ለፈጠረው ሰው በልጁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የዘለዓለም ድኅነትን እንዳዘጋጀ እና እርሱንም እንደ ግል አዳኛቸው አድርገው አምነው ተቀበለው  ኃጢያታቸውን ለሚናዘዙ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጅነትን ሥልጣን እንደሚሰጣቸው ታምናለች።

ዘፍጥረት 17፡1-2፤ ዘፍጥረት 22፡16-18፤ ዘጸአት 3፡15፣ ዘጸአት 6፡2-5፤ የዮሐንስ ወንጌል 1፡29፤ የዮሐንስ ወንጌል 1፡12፤ የዮሐንስ ወንጌል 3፡16፤ ኤፌሶን 4፡6።

ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር አብ ዘላለማዊ ልጅ መሆኑን፡ በመንፈስ ቅዱስ ተፀንሶ በድንግል ማሪያም መወለዱን፡ ፍጹም ሰው እና ፍጹም አምላክ ሆኖ መዋሃዱን፡ ኃጢአት ያልሰራ፡ የኃጢአተኞች ምትክ ሆኖ ከአብ መላኩን፡ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ደሙን በማፍሰስ ለኃጢአተኞች ራሱን ቤዛ አድርጎ፡ ሰውን ዋጅቶ ከእግዚአብሔር ለማስታረቅ ከሞት ተነሥቶ በክብር ማረጉን፡ ለሰው ልጅ ሁሉ ሊማልድ ዘወትር በአባቱ ቀኝ በሕይወት መኖሩን፡ የቤተ ክርስቲያን መስራች እና ራስ መሆኑን፡ ለፍርድም ዳግመኛ ተመልሶ እንደሚመጣም ታምናለች።

ዘፍጥረት 3፡15፤ የማቴዎስ ወንጌል 1፡20-23፤ የዮሐንስ ወንጌል 1፡1-14፤ የሉቃስ ወንጌል 1፡35፤ የሐዋሪያት ሥራ 17፡31፤ ዕብራዊያን 9፡13፡4።

የመንፈስ ቅዱስ መንፈሳዊ ምላተ-አካል እንዳለውና፡ መለኮት መሆኑን፡ ዓለምን ስለ ኃጢአት ስለ ጽድቅና ስለ ፍርድ እንደሚወቅስ በአማኞች ውስጥ አድሮ ወደ እውነት ሁሉ እንደሚመራቸው፡ እንደሚያጽናናቸው፡ የቅድስና ኑሮ ለመኖር እንደሚያስችላቸው፡ ለአገልግሎትም ኃይልን እንዲሁም ለአካሉ ብርታት የፀጋ ስጦታዎችን እንደሚሰጣቸው ታምናለች።

ዘፍጥረት 1፡2፤ የዮሐንስ ወንጌል 16፡7-8፤ የሐዋሪያት ሥራ 1፡18፤ ሮሜ 8፡1-4፤ ገላቲያ 4፡6፤ 2ኛ ጴጥሮስ 1፡21።

መጽሐፍ ቅዱስ ብሉይ እና ሐዲስ ኪዳን በመባል የተሰየሙ በውስጣቸው በቁጥር ስልሳ ስድስት (66) መጽሐፍት በመላው በእግዚአብሔር መንፈስ ተመርተው ቅዱሳን ሰዎች እንደፃፉት በማመን ሰው ሁሉ ሊታመንት የሚገባ የቤተ ክርስቲያን እምነትና እንዲሁም የእግዚአብሔር ስርዓት ምንጭ ደግሞም መለኪያ የሆነ እንደሆነ፤ እንደዚሁም ኃይልና ሥልጣን ያለው ከስህተት የራቀ እውነተኛ የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነ ታምናለች።

ዘሌዋውያን 8፡35-36፤ 2ኛ ሳሙኤል 23፡2፤ መዝሙር 12፡6፤ የማቴዎስ ወንጌል 24፡35፤ የዮሐንስ ወንጌል 17፡17፤ 1ኛ ተሰሎንቄ 2፡3፤ ዕብራውያን 4፡12፤ 2ኛ ጢሞቴዋስ 3፡15-17፤ ያዕቆብ 1፡25፤ የዮሐንስ ራእይ 228-9።

ስለ ሰው ሁሉ ኃጢአት በመስቀል ላይ በመሞት ራሱን ቤዛ አድርጎ በሰጠው ኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ሰው ሁሉ በእግዚአብሔር ፀጋ ብቻ እንደሚድን ታምናለች። እንዲሁም በአምሳሉ ሁሉ የተፈጠረው ሰው በኃጢያቱ፡ ተጸጽቶ ንስኃ በመግባት በመንፈስ ቅዱስ ዳግመኛ ተወልዶ የእግዚአብሔር ልጅነት ሥልጣን እንደሚሰጠው እንዲሁም ደግሞ የክርስቶስም መንፈሳዊ ባረኮትን በመቀበል የዘለዓለም ሕይወትንም እንደሚያገኝ ታምናለች።

ትንቢተ ኢሳያስ 53፡4- 12፤ የዮሐንስ ወንጌል 1፡12-13፤ የሐዋሪያት ሥራ 13፡38-39፤ ሮሜ 3፡20-26፤ ኤፌሶን 2:8-9።

በምትታየውና የማትታየውን ቤተ ክርስቲያን ታምናለች። ኢየሱስ ክርስቶስ የቤተ ክርስቲያን መሰረት እና መስራች እንዲሁም ራስና መሪ አንደሆነ ታምናለች። ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስን በማመን ንስሐ ገብተው ዳግመኛ የተወለዱና መንፈስ ቅዱስም አንድ አካል ያደረጋቸው አማኞች ሁሉ ያሉባት የክርስቶስ አካል መሆንዋን በማመን ለክርስቶስም ቃል በፍጹም መታዘዝ እንዳለባቸው ታምናለች።

የማቴዎስ ወንጌል 16፡18፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 3፡11፤ ኤፈሶን 2፡20-22፤ ኤፌሶን 5፡23፤ ሱብራውያን 3፡1፤ የሐዋሪያት ሥራ 16፡31፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡12-27፣ ገላቲያ 3፡26፤ 1ኛ ጴጥሮስ 2፡9-10።

ኢየሱስ ክርስቶስ የማይሞትና የማይበሰብስ አካል ለብሶ ከሙታን መካከል እንደተነሳ እንዲሁም ጻድቃንና ኃጢአንን በማይሞትና በማይበሰብስ አካል ከሙታን ተነስተው ጻድቃን ወደ ዘለዓለም ደስታ፡ ኃጢአን ደግሞ ወደ ዘለዓለም ስቃይ እንደሚሄዱ ታምናለች።

ትንቢተ ዳንኤል 12:2፤ የዮሐንስ ወንጌል 5፡28-29፤ የዮሐንስ ወንጌል 20፡24-29፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 15፡20-23፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 15፡42-44፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 15፡51-54።

ሰይጣን የሆነው አስቀድሞ ግን ኪሩብ እግዚአብሔር በመጀመሪያ ጥበበኛ ደግሞም ውብ አድርጎት በመፍጠር ፍጹምና ፈጣሪውን የሚያገለግል ታላቅ መልአክ እንደነበር፡ ሆኖም እንደ እግዚአብሔር ታላቅ ለመሆን በነበረው ምኞት ራሱና ሌሎችን መላእክት በማሳሳት ሓጢአት ሰርቶ እንደወደቀ፡ በምድር በእባብ ተመስሎ የመጀመሪያዎቹን ሰዎች በእግዚአብሔር ላይ እንዲያምጹ ያታለለ፡ በባህሪው የረከሰ ሐሰተኛ፡ የኃጢያትና የጥፋት ሁሉ ምንጭ፡ የእግዚአብሔር እና የሰው ልጆች ሁሉ ጠላት፡ የጨለማው ዓለም ገዥ እንደሆነ በመጨረሻም ከተከታዮቹ ጋር ወደ እሳት ባህር እንደሚጣል ታምናለች።

ዘፍጥረት 3፡1-6፤ ትንቢተ ኢሳይያስ 14፡12-15፤ ትንቢተ ሕዝቅኤል 28፡12-19፤ የማቴዎስ ወንጌል 25፡41፤

የማርቆስ ወንጌል 1:27፤ የዮሐንስ ወንጌል 844፤ ኤፌሶን 6፡12፤ 1ኛ ዮሐንስ መልዕክት 5፡19፣ 1ኛ ጴጥሮስ 5፡8፤ የዮሐንስ ራእይ 20፡10።

እግዚአብሔር በመጀመሪያ ሰውን በራሱ መልክ እና አምሳል መልካም አድረጎ ፈጥሮት ሳለ ይህም ሰው በሰይጣን ተታሎ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ በመጣሱ በመንፈሳዊ ሕይወቱ ሙት በመሆኑ፡ ኃጢያተኛ በመሆኑ፡ ከሥጋዊ ሞት እና ከሰይጣን ሥልጣን በታች በመሆኑ፡ ከዚህም ውድቀት ራሱን በራሱ ለማዳን የማይችል ፍጡር እንደሆነ ታምናለች።

ከዘፍጥረት 1፡26-27፤ ዘፍጥረት 2፡17፤ ዘፍጥረት 16፡17፤ ዘፍጥረት 3፡1-22፤ የዮሐንስ ወንጌል 8፡44፤ ሮሜ 5፡6፤ ሮሜ 5፡8፤ ኤፌሶን 2፡1-3፤ ኤፌሶን 2፡12።

በኃጢአታቸው ተፀፅተው በንስሃ በጌታ ያመኑ፡ አማኞች ባመኑበት ወቅት ከሞት ወደ ሕይወት መሸጋገራቸውን ማወቅ አንደሚችሉ፡ እግዚአብሔር ከመውደቅ ሊጠብቃቸው እንደሚችል በቅዱስ ቃሉ የተፃፈ እንደሆነ፡ ሆኖም ከእርሱ ፀጋ ለማደግና ከጌታም ላለመለየት ድኅነታቸውን ለመጠበቅ በእምነት የመታዘዝ ኃላፊነት እንዳለባቸው ታምናለች።

የዮሐንስ ወንጌል 5፡14፤ ሮሜ 8፡16፤ 1ኛ ቆሮንቶt 16፡1-3፤ 1ኛ ጴጥሮስ 3-51፣ እብራውያን 3፡12-19፤ 1ኛ

ዮሐንስ 5፡13፤ ይሁዳ 24-25።

ማንኛውም በጌታ የዳነ ሰው፡ ከዳነበት ቀን ጀምሮ ከዓለማዊነት እንዲሁም በዓለም ውስጥ ካሉት ከንቱ ነገሮች ተለይቶ ለእግዚአብሔር ክብር በኢየሱስ ክርስቶስ የጽድቅ ኑሮ መኖር እንደሚገባው ታምናለች።

የዮሐንስ ወንጌል 17፡15፤ 2ኛ ቆሮንቶስ 6፤14-18፤ቲቶ 2፡11-14።

በክርስቶስ አዳኝነት ያመኑ ሁሉ በእርሱ አንድ ኣካል የመሆናቸው የመንፈስ አንድነት እንዳላቸውም ታምናለች።

ሮሜ 12፡15፣ 1ኛ ቆሮንቶስ 12፡13-26፤ ኤፌሶን 4፡1-7።

የክርስቶስ ዳግም ምጽዓት የአማኞች ሁሉ ተስፋ መሆኑንና በምጽአቱ ጊዜ በሕይወት ያሉና ከሙታን የሚነሱ አማኞች ሁሉ ጌታን ከአየር እንደሚቀበሉት ከዚያም በኋላ ለዘለዓለም በደስታ ከእርሱ ጋር እንደሚኖሩ ታምናለች።

የማቴዎስ ወንጌል 24፡24፣25፣30፣31፣44፤ የማቴዎስ ወንጌል 25፡31፤ የዮሐንስ ወንጌል14፡3፤ የሐዋሪያት ሥራ 1፡11፤ 1ኛ ተሰሎንቄ 4፡13-18፤ 1ኛ ዮሐንስ 2፡28።

ገነት በሞት እና በትንሣኤ መካከል ባለው ጊዜ ጻድቃን ከክርስቶስ ጋር በሰማይ በደስታ የሚኖሩበት ቦታ እንደሆነች ታምናለች።

የሉቃስ ወንጌል 23፡43፤ ፊልጵስዩስ 1፡21-23።

በሞትና ትንሣኤ መካከል ባለው ጊዜ በክርስቶስ አዳኝነት ያላመኑ ሁሉ የሚቆዩበት የስቃይ ቦታ መሆኑን ታምናለች።

የሉቃስ ወንጌል 19፡19-31፤ 2ኛ ጴጥሮስ 2፡10።

መንግሥተ ሰማያት በጌታ ያመኑ አማኞች ለዘለዓለም በዘልአለማዊ ደስታ ከጌታ የሚኖሩት ስፍራ መሆኑን

ታምናለች።

የማቴዎስ ወንጌል 25፡34፤ የዮሐንስ ራእይ 14፡13፤ የዮሐንስ ራእይ 21፡1-7፤ የዮሐንስ ራእይ 22፡1-5።

የእሳት ባሕር አስቀድሞ ለሰይጣን፣ አጋንንቶችና እና በክርስቶስ አምኖ ያልዳኑት ኃጥአተኞች፡ ለዘለዓለም የሚቀጡበት የስቃይ ቦታ መሆኑን ታምናለች።

የማቴዎስ ወንጌል 25፡41፣46፤ የዮሐንስ ራእይ 148-11፤ የዮሐንስ ራእይ 20፡10-15፤ የዮሐንስ ራእይ 21፡8።

SUPPORT OUR MINISTRY